የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተካሄደ – NEAEA


በኤጀንሲው ከሚገኙ ድጋፍ ሰጪ ዳይሬክቶሬቶች አንዱ የሆነው የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ከስራና ከእለት ተዕለት ህይወት ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ድካም መቋቋም (Stress Management), የጊዜ አጠቃቀም(Time Management), ስሜታዊ ልህቀት(Emotional Intellegence), የቡድን ጽንሰ-ሃሳብ(The Concept Of team), በተሰኙ አራት የተለያዩ የስልጠና ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ የአንድ ቀን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና የካቲት 7/2012 ዓ.ም በአዳማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሄዷል፡፡
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርይሁን ዱሬሳ በእለቱ በአራቱም ርዕሰ ጉዳዮች የሚሰጡት ስልጠናዎች ከምንሰራቸው ስራዎች ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ለእያንዳንዱ ፈጻሚ የሚኖራቸውን ፋይዳ ከግንዛቤ በማስገባት ስልጠናውን ሁሉም የኤጀንሲው ሠራተኞች በትኩረት እንዲከታተሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከሳቸው በመቀጠል ስልጠናውን በተመለከተ መልዕክት ያስተላለፉት የኤጀንሲው የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት አስማረ ስራና የህይወት ውጣ ውረድ የሚፈጥሩት አካላዊና አዕምሯዊ ድካም እንዴት መቋቋምና ማስወገድ እንደሚገባ ማወቅ ከስልቹነትና ከተስፋ ቆራጭነት እንዲሁም ከስንፍና ተላቆ በታደሰ መነቋቋት የተሻለ ስራ ለመስራትና ጤናማ ህይወትን ለመምራት ይረዳል ብላዋል፡፡ አክለውም ጊዜ ወርቅ ነው ከሚለው አባባል ተነስቶ ሁሉንም ነገር በጊዜ ለመከወን የሚያስችል ልምድና ችሎታን ማዳበር ለስኬታማነት ቁልፉ ሚስጥር መሆኑን በተጨማሪም በደስታም፣ በሃዘንም፣ በድልም፣ በሽንፈትም፣ በማግኘትም ይሁን በማጣትም ወ.ዘ.ተ……ወቅት ሁሉ ስሜትን በአግባቡ በመግራትና በመቆጣጠር ለተሻለ ህይወት እራስን ማዘጋጀት አዕምሮዊ ብልህነትን የሚጠይቁ ጉዳዮች መሆናቸውን በመግለጽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው እነዚህን ጉዳዮች ያጠቃለለ እውቀቶችን የያዘ በመሆኑ ሠልጣኞች በስልጠናው ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግና ልምዳቸውን በማጋራት ስልጠናው የተዋጣለት እንዲሆን አሳስበው መድረኩን ለአሠልጣኟ ለቀዋል፡፡ አሰልጣኟም ስልጠናውን እጅግ አሳታፊ በሆነ መልኩ ለሠልጣኖች በማቅረብና በስልጠናው ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ሰፋ ያሉ ውይይቶች ተካሂዶባቸውና የጋራ መግባባት ተደረሶባቸው የእለቱ ስልጠና ተጠናቋል፡፡Source link